Back

ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ “የቃል ኪዳን ቤተሰብ” አጀማመር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አደረገ፡፡

**** መስከረም 14/2018 ዓ.ም.****

በሰላም ሚኒስቴር የሚመራው ይህ ትልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ቦንጋ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ወደ ሁሉም የዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው የሚመጡ ተማሪዎች ብቸነት እንዳይሰማቸው ፍቅር እና እንክብካቤን መስጠት ዓላማው ያደረገ በመሆኑ “የቃል ኪዳን ቤተሰብ” መመደቡ አስፈላጊ ሆኗል፡፡

መ/ር አጥናፉ አስፋው የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገ/ት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር “የቃል ኪዳን ቤተሰብ“ ምንነትና ዓላማ ዙሪያ ሰፊ የሆነ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተለይ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አነሳሽነት የተጀመረ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የሀይማኖት አባቶችን ጨምሮ ከሁሉም የቦንጋ ከተማ መዋቅሮች የመጡት ባለድርሻ አካላቱ ፍጹም ደስተኛ እና ፍቃደኝነታቸውን ገልጸው በሰነድ አለመደገፉ እንጂ ቀድመን ስራውን ጀምረናል በማለት ለፕሮጀክቱ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል፡፡

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደገላ ኤርገኖ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ ዩኒቨርሲቲዎች በዋናነት ዕውቀትና እውነት የሚሸመትባቸው መሆኑን አብራርተዋል።

“የጎንደር ቃል-ኪዳን ቤተሰብ” በዋናነት ከኢትዮጵዊነት አንጻር እየተሸረሸሩ ያሉ እሴቶቻችንን በማጎልበት ተማሪዎች አዲስ በሚመደቡበት አካባቢ ያለውን ታሪክ፣ ባህል፣ እና እሴት ጋር ራሳቸውን በማስተዋወቅ ከዕውቀት ግብይቱ ባሻገር ሁለንተናዊ ስብዕናቸው ተገንብቶ የተሟላ ማንነትን መፍጠር ላይ መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በመጨረሻም ቀጣይ መሰራት የሚገቧቸው ተግባራት ላይ ሀላፊነት በመውሰድ ውይይቱ ተቋጭቷል፡፡

በጋራ እንችላለን!