Back

ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ ዘርፍ ያስተማራቸውን  918 ተማሪዎችን ለ6ኛ ጊዜ አስመረቀ።

                  *ሰኔ 14/2017 ዓ.ም
መርሀ-ግብሩ በአባቶች የምረቃ ሥነ-ሥርዓት  የተጀመረ ሲሆን በመቀጠል የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ደገላ ኤርገኖ (ዶ/ር) የቦርድ አመራሮችን እንዲሁም የዕለቱን የክብር እንግዳ እና ከተለያዩ መዋቅር የተጋበዙ አካላትን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ነበር።

በመልዕክታቸው የዩኒቨርስቲው በመማር መስተማር ߹በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት እየሰራ  ያለውን የተለያዩ ተግባራት አብራርተዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ  ክቡር አቶ ማስረሻ በላቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሀላፊ ባስተላለፉት መልእክት የበለጸጉ ሀገራት ዛሬ ለደረሱበት ምዕራፍ ያላቸው በቂ የተማረ የሰው ሀይል መሆኑን ገልጸው መንግስት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም አውስተዋል።

የትምህርት ዘመን የሚጠናቀቅ ሳይሆን የሚቀጥል በመሆኑ የዛሬ ምሩቃንም ወደ ሌላ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሪያ  ጅማሮ መሆኑን አሳስበው ለተመሪቂ ተማሪዎች መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመቀጠል የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ዋና ሬጅስትራር በሀይሉ ገ/ማሪያም (ዶ/ር)  የየኮሌጁን ዲኖች በየተራ በመጋበዝ  ዕጩ ተመራቂዎቻቸውን በክብር እንግዳው߹ በቦርድ አባላትና በዩኒቨርሲቲው የሴኔት አባላት ፊት በማቅረብ እንዲያስመርቋቸው ጋብዘዋል።

የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ሜዳሊ ተሸላሚዎች  የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ አባላት  እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች እጅ  ሽልማታቸውን የተቀበሉ ሲሆን የዋንጫ ተሸላሚዎች ከዕለቱ የክብር እንግዳ ከክበር አቶ ማስረሻ በላቸው እጅ ዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የቦንጋ ዩኒቨርሲት አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አፉወርቅ ካሱ  ለተመራቂ ተማሪዎች ባስተላለፉት የአደራ መልዕክት ተሞክሯቸውን ከማጋራት ባሻገር የመመረቅን ልዩ ስሜት አጋርተው ከዚሁ ጋር አያይዘው የሀገር አደራ መሸከማችሁን እንዳትረሱ ብለዋል፡፡
መማር የማያልቅ እና በዕድሜያችን ሁሌም የሚቀጥል መሆኑም መዘንጋት እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡ በምትሰማሩበት ቦታ ሁሉ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ማሰብ እንዳትረሱ ብለዋል፡፡

በዛሬው የምረቃ ስነ-ስርዓት በቅድመ ምረቃ 845 በድህረ-ምረቃ 73 በአጠቃላይ 918ተማሪዎች ተመርቀዋል።

በመጨረሻም  የኢትዮጵያን ብሔራዊ  ሕዝብ መዝሙር በመዘመር የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ተቋጭቷል፡፡

በጋራ  እንችላለን!